ኢትዮጵያ የ74ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆና ተመረጠችrnየተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ለ74ኛው ጠቅላላ ጉባዔ በፕሬዚዳንትነት እና በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚያገለግሉ ሀገራትን መርጧል። በዚህም ምርጫ ጠቅላላ ጉባዔውን ናይጄሪያ በፕሬዚዳንትነት ኢትዮጵያን ጨምሮ አምስት ሀገራት ደግሞ በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ በሙሉ ድምጽ ተመርጠዋል።rnrnኢትዮጵያ በምክትል ፕሬዚዳንትነት የምታገለግልበትና እ.ኤ.አ. ከመስከረም ወር 2019 ጀምሮ የሚጀመረው 74ኛው ጠቅላላ ጉባዔ በከፍተኛ ደረጃ የተዘጋጁና የሀገራት መሪዎች የሚሳተፉባቸው ታላላቅ ስብሰባዎች የሚካሄዱበት ጉባዔ ነው።rnrnከነዚህ ታላላቅ ጉባዔዎች መካከልም በተመድ ዋና ጸሐፊ አዘጋጅነት የሚካሄደውና እ.ኤ.አ. መስከረም 23 ቀን 2019 የሚደረገው የአየር ንብረት ለውጥ የድርጊት ከፍተኛ ጉባዔ የሚገኝበት ሲሆን ሀገራችን በዋና ጸሀፊው ከተለዩት ዘጠኝ የድርጊት አቅጣጫዎች መሀከል የታዳሽ ኃይል እና የኢነርጂ ሽግግር የድርጊት አቅጣጫን ከዴንማርክ ጋር በጋራ እንድትመራ በመመረጥ ሰፊ ስራዎችን እየሰራችበትና በጠቅላላ ጉባዔው ወቅትም ይህንኑ የመሪነት ሚናዋን የምታሳይበት ይሆናል።rnrnከዚህ ጎን ለጎን እ.ኤ.አ. መስከረም 24 ቀን 2019 በጠቅላላ ጉባዔ ደረጃ የሚደረገው የዘላቂ ልማት ግቦች የፖለቲካ ጉባዔ፣ እ.ኤ.አ. መስከረም 26 ቀን 2019 በጠቅላላ ጉባዔ ደረጃ የሚደረገው የፋይናንስ ለልማት ስብሰባ፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. መስከረም 23 ቀን 2019 የሚካሄደው ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ከፍተኛ ጉባዔ በ74ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ትኩረት የሚሰጣቸው ናቸው።rnrnከእነዚህ ታላላቅ ስብሰባዎች በተጨማሪ ተመራጭ ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች ዓመቱን ሙሉ የሚካሄዱ ስብሰባዎችን የመምራትና የማስተባበር ኃላፊነቶች እንደሚኖርባቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።






